Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ ሰዋስውን ከቅርፁ፣ ከትርጉሙና ከአገልግሎቱ ጋር በማቀናጀት ማስተማር የተማሪዎችን የሰዋስው እውቀት እና የመጻፍ ክሒል ለማሳደግ ያለውን ውጤታማነት መመርመር ነው፡፡ ይህንን ዓላማ ለማሳካትም ስልሳ ተማሪዎች በወሳኝ ንሞና ተመርጠው በሁለት ቡድን በመክፈል ሙከራዊ ጥናት ተካሂዷል፡፡ በሙከራ ቡድንና በቁጥጥር ቡድን ተማሪዎች መካከል ጉልህ የሰዋስው እውቀት እና የመጻፍ ክሒል ልዩነት አለመኖሩን ለማረጋገጥ ቅድመ ፈተና ተሰጥቷል፡፡ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ጉልህ የሰዋስው እውቀት እና የመጻፍ ክሒል ልዩነት እንደሌለ የቅድመ ፈተናው የውጤት ትንተና አመላክቷል፡፡ የቅድመ ፈተና ውጤቱን በማስከተልም ሁለቱ ቡድኖች ከመጻፍ ክሒል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የሰዋስው ትምህርቶችን (የተውላጠ ስሞችን መደብ፣ ጾታ፣ ቁጥርና የተውላጠ ስም አይነቶችን እና የዓረፍተነገር ስልቶችንና የዓረፍተነገር አይነቶችን) በተለያዩ ዘዴዎች ተምረዋል፡፡ የሙከራ ቡድን ተማሪዎች ሰዋስውን ከቅርፁ፣ ከትርጉሙና ከአገልግሎቱ ጋር በማቀናጀት ሲማሩ፣ የሙከራ ቡድን ተማሪዎች ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2007 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በተግባር ላይ ያዋለው የሰባተኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መጽሐፍ በሚያዘው (ቅርፅ ላይ በሚያተኩረው) የሰዋስው ማስተማሪያ ዘዴ ተምረዋል፡፡ የሙከራ ትምህርቱ ለተከታታይ ስድስት ሳምንታት (ለአስራ ስምንት ክፍለ ጊዜዎች) ከተሰጠ በኋላ ድህረ ፈተና ተሰጥቷል፡፡ ውጤቱም በገላጭ ሰታቲስቲክስ እና በባእድ የናሙናዎች ቲ-ቴስት ተተንትኗል፡፡ የትንተናው ውጤት እንዳመለከተውም የሙከራ ቡድን ተማሪዎች ከቁጥጥር ቡድን ተማሪዎች የበለጠ አማካይ ውጤት አስመዝግበዋል፤ ጉልህ የሰዋስው እወቀትና የመጻፍ ክሒል ልዩነት መኖሩም ተረጋግጧል፡፡ በዚህም መሰረት ሰዋስውን ከቅርፁ፣ ከትርጉሙና ከአገልግሎቱ ጋር በማቀናጀት ማስተማር የተማሪዎችን የሰዋስው እውቀት እና የመጻፍ ክሒል ያሳድጋል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ ከዚህ ጥናት የተገኘው ውጤትም Abraham (2008)፣ Werede (1986)፣ Dkhissi (2014) እና Kheider (2015) እንግሊዝኛ ቋንቋን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ በሚማሩ ተማሪዎች ከሰሩት ጥናት ያገኙት ውጤት ጋር ይስማማል፡፡