Abstract:
ይህ ጥናት የጋሞኛ አፈፈት ተማሪዎች አማርኛን እንደ2ኛ ቋንቋ በሚማሩበት ወቅት የሚታየው የቋንቋ ቅየራ ሁኔታ፣ ሚና እና መምህራን ስለ ስልቱ ያላቸውን አተያይ በተመለከተ የተሰራ ነው፡፡ ጥናቱ በጨንቻ ወረዳ ውስጥ የተሰራ ሲሆን በወረዳው በገጠርና በከተማ የሚኖሩ የ5ኛ ክፍል የጋሞኛ አፈፈት ተማሪዎች አማርኛ በሚማሩበት ወቅት ያላቸውን የቋንቋ ቅየራ ሁኔታ አቅርቧል፡፡ ጥናቱ በቅልቅል የምርምር ዘዴ የተሰራ ሲሆን መረጃዎቹም በመቅረጸድምፅ ወምስል በተደረገ ምልከታ እንዲሁም በጽሁፍ ጥያቄ ከመምህራንና ከተማሪዎች ተሰብስበዋል፡፡ አብዛዎቹ መምህራን በቋንቋ ቅየራ ላይ አዎንታዊ አመለካከት እንዳላቸው የጥናቱ ውጤት ያሳያል፡፡ የተወሰኑ መምህራን ግን ቅየራ በቋንቋ መማር ማስተማሩ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚል ስጋት ስላላቸው በክፍል ውስጥ እንደስልት ጥቅም ላይ ሊውል አይገባውም ብለው እንደሚቃወሙ የጥናቱ ውጤት አመላክቷል፡፡ በምልከታ ከተሰበሰበው መረጃ ከሁለቱም ትምህርት ቤቶች በስምንት ክፍለጊዜ ምልከታ 139 ቅየራ ተመዝግቧል፡፡ አብዛኛዎቹ የቋንቋ ቅየራ በቱቱሻ ትምህርት ቤት የተመዘገቡ ሲሆን በዚህ ትምህርት ቤት የታየው በዓረፍተ ነገር ደረጃ ያለው የቅየራ ሁኔታ በጣም በመብዛቱ በትምህርቱ ዓላማ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑን የጥናቱ ትንተና ጠቁሟል፡፡ ስልቱ ለተማሪዎች የተለያዩ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ እነዚህም ያልገባቸውን የቋንቋ ትምህርት ይዘት እንዲጠይቁ፣ በትምህርታቸው ላይ መነሳሳት እንዲኖራቸው እና በቡድን ውይይት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማገዝ መሆናቸውን የትንታኔው ውጤት አሳይቷል፡፡ ለመምህራን ደግሞ አዳዲስ ጽንሰ-ሀሳቦችን፣ ይዘቶችንና የቃላት ፍቺዎችን ለማስተዋወቅ፣ ትዕዛዝ ለማስተላለፍ፣ የክፍሉን ሥነ-ስርዓት ለማስጠበቅና ተማሪዎች እንዲመልሱ ለማበረታታት አገልግሎት ላይ መዋሉን የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡