Abstract:
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ የነበረው በሰባተኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሀፍ ውስጥ አንብቦ የመረዳትና የመጻፍ ክሂል ቅንጅታዊ የይዘት አቀራረብን መተንተን ነው፡፡ይህን ዓላማ ለማሳካትም በሰነድ ፍተሻ፣በጽሁፍ መጠይቅና በቃለ መጠይቅ መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ የጥናቱን መረጃዎች ለመተንተን ገላጭ የመረጃ መተንተኛ ስልት በተግባር ላይ ውሏል፡፡ የተሰበሰበው መረጃ በአግባቡ ተደራጅቶ ትንተና ተደርጎበታል፡፡ከመረጃዎቹ የተገኙት ውጤቶች የሚያመለክቱት አንብቦ የመረዳትና የመጻፍ ክሂልን የሚመለከቱ ይዘቶች አቀራረብ ለመማር ማስተማሩ ሂደትም ሆነ ለተማሪዎቹ ልምምድ አመቺ መሆናቸውን፤ አንብቦ የመረዳትና የመጻፍ ክሂልን የሚመለከቱ ይዘቶችና መልመጃዎች አቀራረብ የተማሪዎችን ደረጃ፣ዕድሜና ችሎታ እንዲሁም ዳራዊ እውቀታቸውን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ መሆናቸውን፤የመማሪያ መጽሀፉ አቀራረብ አንብቦ የመረዳትና የመጻፍ ክሂሎች በተቀናጀ መልኩ እንደተዘጋጁና የማስተማሪያ መሳሪያዎቹ አንብቦ የመረዳትንና የመጻፍ ክሂሎችን አቀናጅቶ ለማስተማር እገዛ እንዳላቸው የጥናቱ ውጤት ያመለክታል፡፡በአንጻሩ አንብቦ መረዳትንና የመጻፍ ክሂሎችን የሚመለከቱ መልመጃዎች አቀራረብ ለትምህርቱ ከተመደበው ሰዓት ጋር ያለመጣጣም ችግሮች መኖራቸውን፣አልፎ አልፎ ስለ መልመጃዎቹ አሰራር ሙሉ መረጃ የማይሰጡ መመሪያዎች በመጽሀፉ ውስጥ መካተታቸውን የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡ከዚህም በተጨማሪ አብዛኛዎቹ መምህራን ስለማንበብና መጻፍ ክሂሎች ቅንጅታዊ አቀራረብ እውቀቱ ቢኖራቸውም ትኩረት ሰጥቶ አቀናጅቶ በማቅረብ ረገድ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ መሆኑን የጥናቱ ውጤት አመልክቷል፡፡በአጠቃላይ በመጽሐፉ ውስጥ በሚገኙ የአንብቦ መረዳት መልመጃዎች
14
አቀራረብ ላይና በመምህራን ቅንጅታዊ አተገባበር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ስልቶች በመፍትሄ ሀሳቦች ስር ተጠቁመዋል፡፡