Abstract:
የጥናቱ ዋና ዓላማ ትብብራዊ መማር ዘዴ የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታ ለማሻሻል ያለው ሚና መመርመር ነው፡፡ ዓላማውንም ለማሳካት ጥናቱ የተከተለው ሙከራዊ ምርምር ሲሆን ከመተንተኛ ዘዴዎች አንጻር ደግሞ መጠናዊ ምርምርን ተከትሏል የጥናቱ ተሳታፊዎችም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየካ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች በዕድገት ጮራ ትምህርት ቤት በ2011ዓ.ም በመማር ላይ ከሚገኙ አጠቃላይ 1034 የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 120 ተጠኚዎች በቀላል ዕጣ ናሙና ዘዴ ከተመረጡ በኋላ በሁለት ቡድን ተመድበዉ ሙከራዊ ጥናቱ ተካሄዷል፡፡በትብብራዊ መማር ዘዴ ከመማራቸው በፊት በሙከራ ቡድኑና በቁጥጥር በድኑ መካከል የመጻፍ ችሎታ ልዩነት መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ፈተና የጽሁፍ መጠይቅ ተሰጥቷል፡፡ በውጤቱም ጉልህ ልዩነት እንደሌለው ተረጋግጧል፡፡ቀጥሎም የሙከራ ቡድን ተማሪዎች ትብብራዊ መማር ዘዴን ለመተግበር የተዘጋጀላቸውን የመለማመጃ ጥያቄዎችን ለተከታታይ አምስት ሳምንታት በሳምንት ሁለት ቀን ከተማሩ በኋላ ድህረ ፈተና ተሰጥቷል፡፡ ውጤቱም በድምዳሜያዊ ገላጭ ስታቲስቲክ በቲ-ቴስት አማካኝነት ተተንትኗል፡፡ የትንተናዉ ዉጤት እንዳመለከተውም የሙከራ ቡድን ተማሪዎች ከቁጥጥር ቡድኑ ተማሪዎች የበለጠ ውጤት አስመዝግበዋል (P=<0.05)፡፡ይህም ውጤት ትብብራዊ መማር ዘዴ የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታ ለማሻሻል ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ በመሆኑም የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታን ለማሻሻል የማስተማሪያ ዘዴዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ከጥናቱ መረዳት ተችሏል፡፡