Abstract:
የዚህ ጥናት አላማ በአማርኛ ቋንቋ ክፍለ ጊዜያት በተማሪዎች የሚጠየቁ ጥያቄዎች
አይነት፣ትምህርታዊና ተግባቦታዊ ፋይዳን መተንተን ነው፡፡ ጥናቱ በአይነታዊ የምርምር
ዘዴ የቀረበ ሲሆን፤አላማዉን ከግብ ለማድረስ የዲስኩር ትንተና ስልትን ተከትሎ
ቀርቧል፡፡ ለዚህ ተግባር ያመች ዘንድ መረጃ በቪዲዩ እና በመቅረጸ ድምጽ ተሰባስቧል፡፡
ቀረጻው የተካሄደው በመንዝ ማማ ወረዳ ሞላሌ ከፍተኛ መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት
ቤት ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ በአመቺ የንሞና ስልት ሲመረጥ ተማሪዎችና መምህራኑ
ደግሞ በአላማ ተኮር የንሞና ስልት ተመርጧል፡፡ ቀረጻውም በተመረጡ ሁለት የ 11ኛ
ክፍል ተማሪዎች ላይ ሲከናወን ለ 5 ክፍለ ጊዜያት ቀረጻ ተከናውኗል፡፡ በቀረጻው
ከተገኘው የ3 ክፍለ ጊዜያት መረጃ በጽሁፋዊ መረጃ መልክ ተቀይሯል፡፡ የትንተናው
ግኝት በአማርኛ ቋንቋ ከሚጠየቁ በርካታ የጥያቄ አይነቶች በቋንቋ ተኮር ጥያቄዎች፣ይዘት
ተኮር ጥያቄዎች፣እውነተኛና ሀሳባዊ ጥያቄዎች እንዲሁም በቅደም ተከተላዊ፣ግጥጥሞሻዊ
እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ጥያቄዎች ላይ ምሳሌዎችን በመስጠት ተተንትኗል፡፡ ሌሎች የጥያቄ
አይነቶች ቢኖሩም አንዱ በሌላው ውስጥ እንዲካተት በማድረግ የቀረበ ጥናት ነው፡፡
በጥናቱ ጥያቄዎች በአይነት ከተቀመጡ በኋላ ያላቸዉን ትምህርታዊና ተግባቦታዊ
አስተዋጽኦ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ትምህርታዊ ፋይዳቸዉ ተማሪዎችን አርቆ
አሳቢ፣አመዛዛኝ፣የሀሳብ አፍላቂ እንዲሁም ጠያቂዎች እንዲሆኑና ልሎችንም ለመግለጽ
ሲሞከር ከተግባቦታዊ ፋይዳቸው አንጻር ደግሞ ተማሪዎች ሀሳባቸውን ሳይጨነቁ
የሚገልጹና ሳይገባቸው የቀረበን ሀሳብ ለመረዳት ተገቢውን ንግግርና ጥያቄ የሚያፈልቁ
እንደሆነ ተቃኝቷል፡፡ በመጨረሻም የማጠቃለያ አስተያየት የቀረበ ሲሆን አስተያቱ
ለቋንቋ መምህራን፣ለመጽሀፍ አዘጋጆችና ለጥናት አድራጊዎች ጥቆማ በመስጠት
ተጠናቋል፡፡